የሀገር ውስጥ ዜና

“አሸባሪው ህወሓት ሕጻናትን ለጦርነት መማገዱ እጅግ ያሳስበኛል” – ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጀራልድ

By Alemayehu Geremew

September 12, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት ሕጻናትን ለጦርነት ሲማግድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዝምታ ማየቱ እጅግ እንደሚያሳስባቸው ፕሮፌሰር አን ፊትዝጌራልድ ገለጹ፡፡

ፕሮፌሰር አን ፊትዝጌራልድ ÷ በካናዳ ዓለም አቀፍ የጸጥታ ጉዳዮች ተመራማሪ እና የባልሲሊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዲን ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር አን ፊትዝጌራልድ ÷ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ጥልቅ ጥናት በማድረግ ውጤት ያመላከቱ የመጀመሪያዋ ተመራማሪ በመሆንም ይታወቃሉ።

ፕሮፌሰር አን ፊትዝጌራልድ ÷ አሸባሪው ህወሓት ለጦርነት ሊማግዳቸው በኃይል የመለመላቸውን እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሕይወታቸው ተርፎ የተማረኩትን ሕጻናት ከ6 ወራት በፊት አግኝተው በማናገር ምስክርነታቸውን በጥናታቸው አካተዋል፡፡

አሁንም አሸባሪው ህወሓት ከመንግስት የቀረበለትን የሠላም አማራጭ ወደ ጎን በመግፋት ሕጻናትን በግዳጅ ለጦርነት በመመልመል መማገዱን ቀጥሏል ብለዋል ፕሮፌሰር አን ፊትዝ፡፡

ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተራድዖ ድርጅቶች በኩል ለኅብረተሰቡ እንዲቀርብ የተላከውን የምግብ እህል እና አልሚ ንጥረ-ነገሮችም ቀጥታ ከተረጂው ህዝቡ አፍ ቀምቶ ለወታደሮቹ እንደሚያውል ፕሮፌሰሯ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

አጥኚዋ ምርምራቸውን ለመስራት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተለይም በአፋር ክልል 5 ወረዳዎች እና በአማራ ክልል ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች መንቀሳቀሳቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ህዝብም በአሸባሪው ህወሓት ተፅዕኖ ሥር መውደቁን አጥኚዋ አልሸሸጉም፡፡

ለጥናት ሲዘዋወሩ በአሸባሪ ቡድኑ በአማራ እና አፋር ክልሎች ተፈፅመው በተመለከቷቸው አሰቃቂ ግድያዎች ልባቸው መሰበሩንም ፕሮፌሰሯ አስረድተዋል፡፡

በክልሎቹ በርካታ ጅምላ መቃብሮችን በዐይናቸው መመልከታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በተለይም በአፋር ክልል ሕጻናት ልጆች ከቤታቸው ተወስደው መገደላቸው ልባቸውን እንደሰበረው ነው የገለጹት፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ፣ የጤና እና የሃይማኖት ተቋማት መውደማቸውን እንዲሁም አገልግሎቶች መቋረጣቸውንም ነው ለጣቢያችን ያስረዱት፡፡

አያይዘውም በከፊል ተቃጥለው ከእሳት የተረፉ የቅዱስ ቁርዓን እና ቅዱስ መጻሕፍ መመልከታቸውን አውስተዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በ2ኛው ዙር ወረራ አፋር እና አማራ ክልሎች ላይ በፈጸመው ጥቃት ከባድ መሣሪያዎችን ፣ ስናይፐርን ጨምሮ ሌሎች ዓይነት ዘመናዊ መሣሪያዎችን መጠቀሙን ገልጸዋል፡፡

ይህም ለክልሎቹ እና ነዋሪዎቹ ጦርነቱን ከባድ እንዳደረገባቸውና አካባቢያቸውን ለቀው እንዲፈናቀሉ እንዳስገደዳቸው አስታውሰዋል፡፡

በአሸባሪው ቡድን ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችም በአፍዴራ እና ሰመራ ማቆያ ጣቢያዎች እንደሰፈሩም ነው ያስታወሱት፡፡

በአፋር ክልል ሲንቀሳቀሱ መንገድ ላይ አንድ ሴት በምጥ ተይዛ ማየታቸውን እና ኋላም አስፋልት ዳር ላይ እንደወለደች ማየታቸውን ነው በማዘን የገለጹት።

በአፋር መጠለያ ጣቢያዎች ሲደርሱም ውሃ አለመኖሩን እና ባዶ የውሃ መያዣ እቃዎችን በሰልፍ ተደርድረው መመልከታቸውን አውስተዋል፡፡

በተመሳሳይ ችግሩ በአማራ ክልል ጋሸና እና ሰሜን ወሎ አካባቢዎች እንደነበረም ነው ያስታወሱት፡፡

ዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙኃን ችግሩ እንዳለ ቢያውቅም ÷ ችግሩን መጥቶ እና ተመልክቶ እውነተኛ መረጃ ከማሰራጨት ይልቅ በተቃራኒው ለሽብርተኛው ቡድን አድልቶ ከሽብርተኛው የሚሰበስባቸውን መረጃዎች እንደሚዘግብም ነው የተናገሩት።

በዚህም ጦርነቱ በአካል ከሚዋጋው አሸባሪው ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጋር እንደሆነ መረዳታቸውን ነው የሚገልጹት።

የተጠና እና የተናበበ ፕሮፖጋንዳ እንዲሁም የሐሰት መረጃዎች ሲሰራጩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከቡድኑ ጋር ሲያብር መመልከታቸው እንዳሳዘናቸውም ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት በሠፊ የምርመራ ጋዜጠኝነት እውነቱን አውጥተው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቢያደርሱ የሚል ምክረ-ሐሳባቸውንም አድርሰውናል፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየሆነ ያለውን ነገር በትክክል እንዲረዳ ሌሎች አጥኚዎችም ተጨማሪ ጥናቶችን እንዲሰሩ መክረዋል፡፡

በወንደሰን አረጋኸኝ እና በዓለማየሁ ገረመው