አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዋግኽምራ ዞን የደሃና ወረዳ እና የአምደ ወርቅ ከተማ አስተዳደር 785 ሺህ ብር የሚገመት የቁም እንስሳት በሠቆጣ ግንባር ለተሠለፈው ጥምር ጦር አበርክተዋል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የደሃና ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዘነበ ማሞ÷ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሠላም ሲል ህይወቱን ለሚሰጠው ሠራዊታችን እስከመጨረሻው ደጀን ሆነን እንዘልቃለን ብለዋል።
አዲሱ አመት ጠላቶቻችን የሚያፍሩበት የኢትዮጵያ የከፍታ ማማ የሚረጋገጥበት አመት እንዲሆንም ተመኝተዋል፡፡
የአምደ ወርቅ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሞገስ ጌታሁን በበኩላቸው÷ በሀገር ጉዳይ የሚመጣን ጠላት ድል ማድረግ ለሠራዊቱ ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ዞን የጉባ ላፍቶ ወረዳ የሳንቃ ከተማ በራያ ግንባር ለሚገኘው ጥምር ጦር ድጋፍ አድርጓል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ሁለት ሰንጋ፣ በጎች ፣ለእለት ምግብ የሚሆን የበሶ ዱቄት፣ ዳቦ ፣ወተት እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ነው ድጋፍ ያደረጉት፡፡
ድጋፉ የተደረገው ጥምር ጦሩ በሚገኝበት ግንባር በመገኘት ነው።
በለይኩን አለም