አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማትን ለማጎልበት በትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰው ሀብት ልማት ዕድገት ሪፖርት አመላከተ።
የ2021/22 ዓለም አቀፍ የሰው ሀብት ልማት አመላካች ሪፖርት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሆኗል።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የዋጋ ግሽበትና መሰል ችግሮች በዓለም አገራት የሰው ሀብት ልማት ዕድገት ላይ ተጽዕኖ መፍጠራቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዳይሬክተር ቱርሃን ሳለህ÷ 90 ከመቶ በላይ የሚሆኑ የዓለም ሀገራት የሰው ሀብት ልማት የዕድገት ምጣኔ መቀነሱን ሪፖርቱ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ተጽዕኖ ውስጥ ሆና ደረጃዋን ማስጠበቋን አድንቀው÷የሰው ሀብት ልማት ዕድገትን ለማረጋገጥ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል እንዳለባት ነው የጠቆሙት፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍና የውስጥ ጫናዎች ቢያጋጥሟትም በትምህርትና በጤና ዘርፎች ላይ የተሰሩ ተግባራት የሰው ሀብት ልማት ደረጃዋን እንድታስቀጥል ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
በቀጣይም በሁሉም የሰው ሀብት የልማት ዕድገት ማረጋገጫ ዘርፎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ የልማት አጀንዳዎቿን ለማሳካት በምታደረገው ጥረት ሁሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል።