አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ ለ2015 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር ዝግጅት ማጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ የምገባ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አንቺነሽ ተስፋዬ ÷ከተማ አስተዳደሩ ከ4 ቢሊየን ብር በላይ በጀት እንደፈቀደላቸውም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ይህም ከባለፉት ዓመታት አንጻር ሲታይ የ20 በመቶ ጭማሪ እንዳለው፤ምግብ የሚያዘጋጁ እናቶች ግብዓቶችን ቀጥታ ከአምራቹ እንዲያገኙ መደረጉንም ገልጸዋል።
እንደ ከዚህ ቀደሙ የተለያዩ አካላት ለተማሪዎች ምገባ መርሐግብር የሚውል ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።
ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በባለሙያ ዝግጅት ተጠናቆልም ነው ያሉት፡፡
እንዲሁም የተማሪ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል በመገመት ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡
በሲሳይ ጌትነት