ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ ለዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤል ከሰጠች ሩሲያ ራሷን ለመከላከል የትኛውንም አማራጭ እንደምትጠቀም አስታወቀች

By Melaku Gedif

September 16, 2022

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ለዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤል ድጋፍ የምታደርግ ከሆነ ሩሲያ ራሷን ለመከላከል የትኛውንም አማራጭ እጠቀማለሁ ስትል አስጠነቀቀች፡፡

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማርያ ዛካሪቫስ እንደገለጹት÷አሜሪካ ከዓለም አቀፍ ህግ ውጪ ለዩክሬን መጠነ ሰፊ የጦር መሳሪያ በማቅረብ የጦር ወንጀል እየፈጸመች ነው፡፡

ዋሺንግተን በዚህ ድርጊቷ ገፍታ ለኪዬቭ የረጅም ርቀት ሚሳአኤል የምታቀርብ ከሆነም ቀይ መስመር እንዳለፈች እና በግጭቱ በቀጥታ እንደተሳተፍች እንቆጥረዋልን ነው ያሉት።

ሞስኮ ራሷን ለመከላከል እና ሉዓላዊነቷን ለማስከበርም የትኛውንም አማራጭ ለመጠቀም የምትገደድ መሆኗን ነው ቃል አቀባዩ ያሳወቁት፡፡

ማርያ ዛካሪቫስ አሜሪካ እስካሁን ኤም-142 እና እና ኤም-270 የተሰኙ እና በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የተመረጡ ዒላማዎችን መምታት የሚችሉ ሮኬቶችን ለዩክሬን እንዳስታጠቀች ማንሳታቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡

ቃላ አቀባዩ አሜሪካ በሩሲያ- ዩክሬን ግጭት ውስጥ ጣልቃ በመግባት ቀጠናውን የማተራማስ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው÷ በአካባቢው አላስፈላጊ የጦር መሳሪያ ውድድር ውስጥ መግባቷንም ጠቁመዋል፡፡

ዩክሬን አሜሪካ በምታስታጥቃት የጦር መሳሪያ ለምታደርሰው ጥቃት አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድም ዘመኑን የዋጀ እና አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጓን አስታውቀዋል፡፡