የሀገር ውስጥ ዜና

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ወደ ሠላም የምታደርገውን ጉዞ ከመደገፍ ውጪ ጣልቃ ሊገባ አይገባም – አምባሳደር ሂሩት

By Alemayehu Geremew

September 17, 2022

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የምታደርገው የሠላም ጥረት ከአቅም በላይ እንዳልሆነና ከድጋፍ ውጪ ያለውን የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብነት እንደማይሻ በቤልጂየም እና በአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ገለጹ።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያውያን የሚሳሱለት የሠላም ጥረት ላይ ሐሳብ በመጨመር ብቻ ሊደግፍ ይችላል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን ሠላምና ደኅንነትን የማስጠበቅ ኅገ-መንግስታዊ ሥልጣን እንዳለው ሊገነዘብ ይገባልም ነው ያሉት።

አምባሳደሯ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ብለው ያነሷቸው ÷የአፍሪካ ኅብረት የጀመረውን የሠላም ሂደት መቀጠል እና በቀጣይ ሁሉንም የፖለቲካ ተዋናዮች የሚያቅፍ ሀገራዊ ውይይት ማካሄድ የሚሉት ሐሳቦች ናቸው።

አሸባሪው ህወሓት ከገባበት አውዳሚ የግጭት ዑደቶች ወጥቶ ውይይትን ሊመርጥ እንደሚገባም ነው የመከሩት።

መንግስት ያወጀው የሰብዓዊ ተኩስ አቁም አሸባሪው ህወሓት የተሰጠውን የሠላም “የወይራ ዝንጣፊ” በመርገጥ በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት በመፈፀም እንዳጨናገፈው አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ዘ ብራስልስ ታይምስ ላይ ባወጡት ፅሁፋቸው ጠቁመዋል።

አሸባሪው ህወሓት የቀረበለትን የሰብዓዊ ተኩስ አቁም እስከሚረግጥ እና ጥቃት እስከሚፈፅም ድረስ ላለፉት አምስት ወራትም የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላም ይፈታል የሚል ተሥፋ እያደገ መጥቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከፈረንጆቹ መጋቢት 24 ቀን 2022 ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግስት የታወጀው የአንድ ወገን የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ስምምነት የመላው ኢትዮጵያውያንን ተስፋ ከፍ ያደረገ እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡

ነገር ግን አሸባሪው ቡድን የሠላም አማራጩን በመርገጥ ከፈረንጆቹ ነሐሴ 24 ቀን 2022 ጀምሮ በአማራ እና አፋር ክልሎች ጥቃት መፈጸሙን አውስተዋል፡፡

በዚህም መንግስት ያወጀው የአንድ ወገን የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ሥምምነት እንዳበቃ እና ወደ ግጭት እንደተገባ አስረድተዋል፡፡

አሁንም ቢሆን አሸባሪ ቡድኑ ወደ ቀልቡ ተመልሶ በአፍሪካ ኅብረት የተጀመረውን የሠላም አማራጭ እንዲቀበል እና ለተፈጻሚነቱም ቁርጠኝነቱን እንዲያሳይ አሳስበዋል።

በዓለማየሁ ገረመው