የሀገር ውስጥ ዜና

የትግራይ ህዝብ አሸባሪውን ህወሓት በቃህ ሊለው እንደሚገባ በቁጥጥር ስር የዋሉ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ተናገሩ

By Mikias Ayele

September 18, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ህዝብ አሸባሪውን ህወሓት በቃህ ሊለው ይገባል ሲሉ በመከላከያ ሰራዊት በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ተናገሩ፡፡

በማይጠምሪ  ግንባር በመከላከያ ሰራዊት  ቁጥጥር ስር ከዋሉ  የሽብር  ጥቃት ለመፈጸም  በአሸባሪው ህወሓት ተልዕኮ ወስደው ከመጡ ታጣቂዎች  መካከል የ45 ዓመቱ ሀዱሽ ታፈረ ሃይለ ማርያም ይገኝበታል።

ሀዱሽ በጥቅምት 2013 ዓም ከሚሰራበት የግብርና ስራ ከባሀከር በታጣቂዎች ተይዞ ወደ ውጊያ እንዳስገቡት ይናገራል።

በኋላም ከቡድኑ በማምለጥ ወደ ሽሬ ከሄደ በኋላ በድጋሚ ተይዞ ወደ ውጊያ አስገብተውት እንደነበር እና ለ3ኛ ጊዜ ጠፍቶ መቀሌ ወደሚገኙት ቤተሰቦቹ ቢመለስም ተይዞ በድጋሚ ወደ ማይጠምሪ ግንባር መግባቱን ገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት በየአውደ ውጊያው በርካታ የትግራይ ወጣት እያለቀ ነው የሚለው ሀዱሽ÷ የትግራይ ህዝብ የህውሓት አሸባሪ ቡድን  በቃህ ሊለው ይገባል ብሏል፡፡

የመኪና አሽከርካሪ ነበርኩ የሚለው ሌላኛው ወጣት ዕቁባይ ገብረ መድህን ደግሞ÷ የሽብር ቡደኑን ለመሸሽ   ከቤተሰቦቹ ጠፍቶ  ወደ ሌላ ቦታ ቢሄድም አባቱ በመታሰሩ ምክንያት የሽብር ቡድኑን እንደተቀላቀለ አስረደቷል፡፡

በማይጠምሪ ግንባር ሀዱሽ እና ዕቁባይን ጨምሮ በርካታ አሸባሪው ህወሓት አሰልጥኖ ለሽብር ጥቃት የላካቸው ታጣቂዎች  በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉ  የሽበር ቡድኑ ህወሓት ታጣቂዎች  እየተደረገላቸው ስለሚገኘው እንክብካቤ አመስግነው÷ ሌሎች ለሽብር ቡድኑ የተሰለፉ  ጓደኞቻቸው እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡