አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2015 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት በተገቢው መንገድ መጀመሩን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡
በተለይ በዘንድሮው ዓመት የአዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት የሚጀመርበት እንደመሆኑ፥ ትምህርት ቤቶች ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተመልክተናል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተመለከታቸው የዕድገት በኅብረት ቅድመ መጀመሪያ፣ አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የልቤ ፋና ቅድመ መጀመሪያ፣ አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያ ቀን ይመጣሉ ተብሎ ከተጠበቀው ተማሪዎች በላይ በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘታቸውን መታዘብ ችሏል።
ለመጡ ተማሪዎችም የትምህርት ቁሳቁስ የመስጠትና ትምህርቱን በተገቢው መንገድ እንዲጀመር መደረጉንም ነው መታዘብ የቻለው።
አዲሱ ሥርዓተ -ትምህርት ተግባራዊ የሚደረግበት የትምህርት ዘመን በመሆኑ የተቀበሉትን መጽሐፍት አዘጋጅተው ለትምህርት ዝግጁ አድርገዋል።
አስተያየት የሰጡ ተማሪዎችም ለአዲሱ ትምህርት ዘመን ዝግጅት ማድረጋቸውንና ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ብዙ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
በሃይማኖት ኢያሱ