አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በዓለም አቀፍ የሳይንስ ውድድር ለግማሽ ፍጻሜ ከተለዩት ምርጥ 30 ተወዳዳሪዎች ውስጥ የተካተተው የ18 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ አቤል አሰፋ ምርጥ 15 ውስጥ ለመካተት እየተወዳደረ ነው፡፡
ውድድሩ ‘ብሬክስሩ’ በተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት በየዓመቱ ተዘጋጅቶ የሚካሄድ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
በዚህ የፈረንጆች ዓመትም 2 ሺህ 400 ተወዳዳሪዎች ለመሳተፍ አመልክተው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
ውድድሩ ውስብስብና ጥልቅ የሆኑ የሳይንስ፣ የሒሳብ እና የፊዚክስ ጽንሰ ሐሳቦችን ምንም የሳይንስ እውቀት የሌላቸው ሰዎች በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉት መልኩ በ90 ሰከንድ በቪዲዮ ማቅረብ ነው።
አቤል አሰፋም “በከባቢ ያሉ ተደርበው የሚገቡ ድምጾችን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል” የሚያስረዳ በሳይንሱ ‘ኖይዝ ካንስሌሽን’ የሚባለውን ጽንሰ ሃሳብ በቪዲዮ ሰርቶ አቅርቧል።
“ብሬክስሩ” የተሰኘው ግብረ-ሠናይ ድርጅትም የአቤል አሰፋን ቪዲዮ ጨምሮ በዙሩ የተመረጡ ቪዲዮዎችን በድርጅቱ የፌስቡክ ገጽ እና የዩቲዩብ ቻናል ላይ ሕዝብ ድምጽ እንዲሰጥባቸው ጭኗል።
በፌስቡክ እና በዩቲዩብ ላይ ከተጫኑት ቪዲዮዎች ከፍተኛ የሕዝብ ድምጽ (ብዙ ላይክ) ያገኘለት ተወዳዳሪ ወደ ምርጥ 15 ተፎካካሪነት ይገባልም ነው የተባለው።
ለዚህ ዙር የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እስከ ሰኞ መስከረም 09/2014 ዓ.ም. ድረስ የሚቀጥል ሲሆን በቀጣዩ ቀንም ወደ ምርጥ 15ቱ ውስጥ የተካተቱ ሥራዎች ይፋ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በውድድሩ አሸናፊ የሚሆነው ተወዳዳሪ፣ የ250 ሺህ ዶላር የትምህርት ዕድል ሽልማት የሚያገኝ ሲሆን፣ አሸናፊው/አሸናፊዋን ተማሪ ለፈጠራ ሥራ ያነሳሳ የሳይንስ መምህር/መምህርት ደግሞ የ50 ሺህ ዶላር ሽልማት ይበረከትላቸዋል፡፡
በተጨማሪም አሸናፊው ትምህርት ቤት የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደሚበረከትለት ነው የተመለከተው።
በዚህ ውድድር አቤል አሰፋ የውድድሩ አሸናፊ እንደሚሆን ተሥፋ ተጥሎበታል፡፡
ለአቤል አሰፋ ድምፅ መሆን ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ ሥራውን መመልከት እና “ላይክ” ማድረግ ይችላሉ፡፡
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=PzTAhCHoIMQ ፌስቡክ https://www.facebook.com/watch/?v=595860615362156
በዘንድሮው ‘ብሬክስሩ ቻሌንጅ’ ምርጥ 30ዎቹ ውስጥ ከተካተቱት ተማሪዎች ውስጥ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከቺሊ፣ ከቻይና፣ ከክሮሺያ፣ ከሕንድ፣ ከኢራቅ፣ ከኒው ዚላንድ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከትሪንዳድ እና ቶቤጎ፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከዩናይትድ ኪንግደም ይገኙበታል።
ከሁለት ዓመት በፊት አንዲት ኢትዮጵያዊት ተማሪ አሸንፋ እንደነበር የሚያስታውሰው አቤል፣ በዘንድሮው ዓመት ግን ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ተወዳዳሪ እርሱ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል።