የሀገር ውስጥ ዜና

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ሲካሄድ የነበረው የምርመራ ሂደት በአብዛኛው ተጠናቀቀ

By Meseret Awoke

September 20, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ሲካሄድ የነበረው የምርመራ ሂደት በአብዛኛው መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በተከሰተው ግጭት አውድ ውስጥ፤ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ከማጣራት፣ ተጎጂዎችን ከመጠበቅና ከመደገፍ አንጻር ስራዎችን ለማስተባበር የተቋቋመውየሚኒስትሮች ግብረ ሃይል አራተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በመድረኩም በግጭቱ ወቅት በአፋርና በአማራ ክልሎች በሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ሲካሄድ የነበረው የምርመራ ሂደት በአብዛኛው መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

ወደ ክስ ሂደት ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን የግብረ ሃይሉ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ታደሰ ካሳ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በምርመራና በክስ ኮሚቴ የሚመራው 158 አባላት ያሉት የምርመራ ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራት ዝርዝር ሪፖርት ለመድረኩ አቅርበዋል፡፡

ወንጀሎች በምን አይነት መልክ እንደተፈጸሙና የምርመራ ግኝቶቹም ምን ምን እንደሆኑ በሪፖርታቸው ላይ አካተው ማቅረባቸውም ነው የተገለጸው፡፡

ቡድኑ በምርመራ ወቅት የተለያዩ ማስረጃዎችን በቪዲዮና በዶክመንት አደራጅቶ መያዙ የተገለጸ ሲሆን ፥ በጦርነት አውድ ውስጥ በርካታ ንጹሃን ላይ ያለፍርድ ስለተፈጸሙ የግድያ ወንጀሎች፣ ከባድ የአካል ጉዳትና በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ስለተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች እንዲሁም በግዳጅ የመሰወር ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው በሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል፡፡

በንብረት ላይ የደረሱ ጉዳቶችም በምርመራ ግኝቱ ላይ መካተታቸውን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!