የሀገር ውስጥ ዜና

የቻይና ዓለም አቀፍ የልማት ኢኒሼቲቭ የልማት ግቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ወሳኝ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

By ዮሐንስ ደርበው

September 21, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለመተግበር ትብብር እና አጋርነት ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

አቶ ደመቀ በኒውዮርክ ከተማ እየተካሄደ ካለው 77ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የዓለም አቀፍ ልማት ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ቡድኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ከማስተዋወቅ አንጻር ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ዕቅዶች ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ፥ ሁለንተናዊው ዓለም አቀፍ የልማት ኢኒሼቲቭ የጋራ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚረዳ አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ሽግግሩን ለማፋጠን በሚደረግ ጥረት አይተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።