የሀገር ውስጥ ዜና

የታዳጊ እና የባሕር በር የሌላቸው አገራት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

By Shambel Mihret

September 23, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ተሳትፎ የምታደርግበት የታዳጊ አገራት እና የባህር በር የሌላቸው አገራት ከፍተኛ የምክክር መድረክ በኒውዮርክ እየተካሄደ ነው፡፡

በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 77ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን ነው ከፍተኛ የምክክር መድረኩ እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

በምክክሩ ላይ አገራቱ እያጋጠሟቸው ያሉ ችግሮችን በትብብር እና በመደጋገፍ መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ትብብርን ለማበረታታት እና የጋራ ዘላቂ ልማት ለማሳካት የንግድ እና የትራንስፖርት ችግሮችን ለመቀነስ ከስምምነት ተደርሷል ተብሏል፡፡

የዚህ ቡድን አባል ኢትዮጵያም በውይይቱ እየተሳተፈች መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያን አቋም ያቀረቡት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አቶ አየለ ሊሬ÷ የባሕር በር የሌላቸው አገራት በኮቪድ-19 ፣በአየር ንብረት ለውጥ፣ በምግብ፣በኢነርጂ እና ፋይናንስ ቀውስ እየተፈተኑ ነው ብለዋል።

አገራቱ እያጋጠማቸው ያለውን ችግር ለመፍታት ከአሁን በፊት የተቀመጠውን የዶሃ ፕሮግራም ትግበራ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የዱኃ የትግበራ ፕሮግራም ፈጣን ለሆነ ዘላቂ እና አካታች የማገገሚያ እና መቋቋሚያ መንገዶች ትኩረት መስጠቱን ታበረታታለች ነው ያሉት።

አቶ አየለ ዶሃ የትግበራ ፕሮግራም በመተማመን እና እውነተኛ ቁርጠኝነት በማሳየት ከልማት አጋሮች ጋር መተግበር ይገባዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ አዘጋጅታ በድህነት ቀነሳ፣ ሥራ ፈጠራ፣ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ሰላም እና መልካም አስተዳደርን ለማሻሻል እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመከላከልም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በመተግበር 25 ቢሊየን ችግኝ መተከሉንም ተናግረዋል።