የሀገር ውስጥ ዜና

የ8ኛ ክፍል ክልላዊና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መርሃ ግብር ወደፊት ይገለጻል- ትምህርት ሚኒስቴር

By Tibebu Kebede

March 19, 2020

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበት መርሃ ግብር ወደፊት እንደሚገለጽ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፥ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝን ለመግታት የቅድመ መደበኛ፣ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የጎልማሶች ትምህርት ተማሪዎች ሊያደርጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በመግለጫቸው፥ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እስከ መጋቢት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለ15 ቀናት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የተዘጉትን የትምህርት ቀናት ለማካካስ ተማሪዎች ላይ ምንም ዓይነት ጫና ሳያድር፣ የትምህርት አመራሮች፣ መምህራንና ማህበረሰቡ በሚወጣው የጊዜ መርሃ-ግብር በመመራት ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም እንደሚያካክሱ አስታውቀዋል።

የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን በተመለከተም፥ በተዘጉት የትምህርት ቀናት በቤታቸው ዝግጅታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበው፤ የፈተና ወቅት መርሃ ግብሩን ወደፊት ይገለጻል ብለዋል።

ሚኒስትሩ ከሚኒስትር ዲኤታዎች፣ የተማሪ ወላጅና የመምህራን ማህበር አመራሮች ጋር በመሆን የእጅ መታጠብ ስነ ስርዓት በማከናወን፤ ተማሪዎች ከኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ራሳቸውንና ማህበረሰባቸውን እንዲከላከሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision