አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች መላው ኢትዮጵውያን ድጋፍ በማድረግ የእምነት ግዴታቸውን እንዲወጡ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡
ጥሪው የቀረበው “ለወገን በመድረስ የእምነት ግዴታችንን እንወጣ” በሚል መሪ ቃል የሃይማኖት አባቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
በመግለጫው በጦርነቱ እንዲሁም ከተፈጥሮ ክስተት ጋር በተያያዘ በድርቁ ሳቢያ ሴቶች፣ ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያንን ጨምሮ በርካታ ወገኖች ለተደራራቢ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ጉዳት መዳረጋቸውን፣ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውንና ዜጎችም መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የወገኖችን ህይወት ለመታደግ ብሎም የሀገርን ሰላም ለመመለስና እየተስተዋሉ ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች እንዲፈቱ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በተለይም የሃይማኖት አባቶች ሚና እጅግ የላቀ ነው ተብሏል፡፡
የሃይማኖት አባቶች የየቤተ – እምነቱ ተከታዮች ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች በመድረስ ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለዚህም የሃይማኖት አባቶች ከኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንዲያስችል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ቁጥር 1000496459001 መከፈቱን ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!