አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ በዓል የምስጋና ቀን በመሆኑ በምስጋና እያከበርን ነው ሲሉ በቢሾፍቱ ተገኝተው እያከበሩ እንደሚገኙ የበዓሉ ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡
የዘንድሮ የሆረ ሀርሰዴ በዓል አባገዳዎች የኢሬፈና ስነስርዓት በማካሄድ በይፋ አስጀምረውታል፡፡
በመርሐ ግብሩ አባገዳዎች ስለሀገር ሰላም ፈጣሪን ጠይቀዋል ፥ ሀገር ሰላም እንዲሆንና መልካም ነገሮች ሁሉ እንዲሆን መርቀዋል፡፡
በዚህ በዓል ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንግዶችን ጨምሮ የቢሾፍቱ ነዋሪዎች እየተሳተፉ ነው የሚገኙት፡፡
በበዓሉ የተገኙት የበዓሉ ተሳታፊዎችም በዓሉ የምስጋና ቀን በመሆኑ በምስጋና እያከበርን እንገኛለን ሲሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
አክለውም በዓሉ በሰላም እየተከበረ እንደሆነ ገልጸው ፥ ህዝቡ ባህሉን በሚያሳይ መልኩና በመተባበርና በመከባበር እያሳለፈ እንደሚገኝም ነው ያነሱት፡፡
የኦሮሞ ህዝብ መገለጫ የሆነው ኢሬቻ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀና ባህሉን በጠበቀ መልኩ እየተከበረ መምጣቱንም አንስተዋል ተሳታፊዎቹ፡፡
ከአሁን በፊት ህዝቡ በዓሉን በነጻነት እንዳያከብር ጫና ሲደረግበት የነበረ እንደሆነ የገለጹት ተሳታፊዎቹ ፥ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ህዝብ ዋጋ የከፈለለትን ነጻነቱን በኢሬቻ አከባበር ላይ ምስጋና በማቅረብ እያሳየ እንደሚገኝም ነው የጠቀሱት፡፡
በመሰረት አወቀ
ምስል በአብርሃም ፈቀደ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!