አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛምቢያዊው የብራይተን የመሐል ሜዳ ተጫዋች ኢኖክ ምዌፑ ባጋጠመው የልብ ሕመም በ24 ዓመቱ ከእግር ኳስ ዓለም ሊገለል መሆኑ ተሰማ፡፡
ምዌፑ ከቤተሰብ በዘር ሊተላለፍ በሚችል የልብ ሕመም ምክንያት ከእግር ኳስ ዓለም እንደሚርቅ ክለቡ አስታውቋል።
እግር ኳስ መጫወቱን የማያቆም ከሆነ ለሕይወቱ አስጊ መሆኑንም ነው የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ የገለጸው።፡
ምዌፑ ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ወደ ማሊ በተጓዘበት ወቅት ሕመም አጋጥሞት እንደነበርም ነው የተነገረው፡፡
ባሳለፍነው ወርም ወደ ምዕራብ አፍሪካ ተንቀሳቅሶ በነበረበት ወቅት ሕመሙ ተቀስቅሶበት ልምምድ ማድረግ እንደተቸገረና ለአራት ቀናት ሆስፒታል እንደቆየ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ወደ እንግሊዝ ተመልሶም ባደረገው የጤና ምርመራ የምዌፑ ብቸኛ አማራጭ ራሱን ከእግር ኳስ ማግለል ብቻ መሆኑን እንደተነገረው የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ይፋ አድርጓል።
ምዌፑ ከዚህ በኋላ እግር ኳስ መጫወት የማያቆም ከሆነ ሕይወቱን ሊያጣ እንደሚችልም ቁርጡ ተነግሮታል ነው የተባለው፡፡
በፈረንጆቹ ሐምሌ 2021 በአራት ዓመት የኮንትራት ውል ከሬድቡል ሳልዝበርግ ብራይተንን በ18 ሚሊየን ፓውንድ መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡
ዛምቢያዊው አማካይም በትዊተር ገጹ በአስገዳጅ ምክንያት ከእግር ኳስ ዓለም እንደሚገለል አስታውቋል።
“ህልሜ መቋጫው ላይ ደርሷል” ያለው ምዌፑ “ከተጫዋችነት ብርቅም ከእግር ኳሱ ዓለም ግን በተጫዋችነትም ባይሆን አልጠፋም” ሲል ገልጿል።
“እየተከፋሁ ከተጫዋችነት እርቃለሁ” የሚለው ወጣቱ አማካይ “በእግር ኳስ ህይወቴ ከጎኔ ለነበሩ ሁሉ ምስጋናየ ይድረሳቸው” ብሏል።
ተጫዋቹ በተለያዩ ክለቦች በነበረው ቆይታ በ170 ጨዋታዎች 27 ጎሎችን ሲያስቆጥር 31 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ደግሞ አመቻችቶ አቀብሏል።
ለዛምቢያ ብሄራዊ ቡድንም 23 ጨዋታዎችን አድርጓል።