ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ ከነዳጅ ክምችቷ 15 ሚሊየን በርሜል ለገበያ ልታቀርብ ነው

By Alemayehu Geremew

October 19, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የነዳጅ አምራች እና ላኪ ሀገራት (ኦፔክ) የሚያቀርቡትን ነዳጅ ለመቀነስ መስማማታቸውን ተከትሎ አሜሪካ ከነዳጅ ክምችቷ 15 ሚሊየን በርሜል ወደ ገበያ ልትለቅ መሆኑን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስታውቀዋል።

የኦፔክ አባል ሃገራት ለዓለም አቀፉ ገበያ የሚያቀርቡትን የነዳጅ መጠን አቅርቦት በቀን በ2 ሚሊየን በርሜል ለመቀነስ መሥማማታቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ባይደን ከአሜሪካ መጠባበቂያ የነዳጅ ክምችት 15 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ ለገበያ ለማቅረብ አቅደዋል።

የነዳጅ እቀባ እና የዋጋ መናሩ የማይረግብ ከሆነም አሜሪካ ተጨማሪ የነዳጅ አቅርቦት ወደ ገበያው ልታሰራጭ እንደምትችል ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ÷ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ67 እስከ 72 ዶላር ዝቅ በሚልበት ወቅት የአሜሪካ መንግስት አሁን ከክምችቱ ያወጣውን የነዳጅ መጠን እንደሚመልስ መናገራቸውን ቲ አር ቲ ወርልድ ዘግቧል፡፡

በአሜሪካ የነዳጅ ዋጋ በእጅጉ መናሩን የአሜሪካ አውቶሞቢል ማህበር አስታውቋል።

አሁን አሜሪካ ከመጠባበቂያ የነዳጅ ክምችቷ ለገበያ አቀርበዋለሁ ያለችው 15 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ በአሜሪካ የአንድ ቀን ፍጆታን የመሸፈን አቅም እንደሌለው የአሜሪካ የሃይል መረጃ አስተዳደርን ዋቢ ያደረገው ዘገባ ያመላክታል።