አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጤና እክል እያስከተለ መሆኑን ባለሙያዎች አስታወቁ፡፡
የዓለም የጤና ድርጅትን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ 99 ባለሙያዎች ይፋ ባደረጉት የጥናት ውጤት፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዓለም በከሰልና ነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ መሆኗ የምግብ ዋስትና ችግር፣ ተላላፊና ከሙቀት ጋር በተያያዙ በሽታዎች የመጋለጥ እድል እንዲጨምር ማድረጉን የጥናት ውጤቱ አመላክቷል።
እንደ ጥናት ውጤቱ ከሆነ ዓለም ላይ ከሙቀት ጋር በተያያዘ የሚከሰት የሞት መጠን በ2/3 ጨምሯል።
የሙቀት መጨመርና የአየር ንብረት ብክለት ለልብና የመተንፈሻ አካላት ችግርን ጨምሮ ለጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ እንዲሁም ለአዕምሮ ጤና መቃወስ ምክንያት ሆነዋል ነው የተባለው።
ሆኖም ጥናቱ አሁንም ችግሮች እንዳሉ ሆነው የዓለም ሀገራት የተፈጥሮን ስነምህዳር በአግባቡ ለመጠበቅ በፍጥነት እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ የብዙ ሚሊየን ሰዎችን ህይወት ማትረፍ ይቻላል ብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፥ የዓለም መሪዎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚወስዱት እርምጃ ከችግሩ ጋር የተመጣጠነ መሆን እንዳለበት መክረዋል፡፡
የዓለም መሪዎች በሚቀጥለው ወር በግብፅ በአየር ንብረት ለውጥ ተገናኝተው እንደሚመክሩ የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።