አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት በኢፌዲሪ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነት አስመልክተው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የደስታ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
በመልዕክታቸውም÷ ኢትዮጵያ የሁላችን ናትና አለመግባባታችንን በውይይት ፈትተን እርቁን እውነተኛ ልናደርገው ይገባል ብለዋል፡፡
ሰላም የሰው ልጆች ሕይወታዊ ሀብት እና ለዚህች ዓለምም አንድ ዐይን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መሪ በዙፋኑ ጳጳስ በመንበሩ፤ ዜጋ በአገሩ ገበሬ በምድሩ፤ የሚኖረው ሰላም ሲሆን ነው ያሉት ቅዱስነታቸው÷ ሰላምንና እርቅን በመስማታችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል፡፡
ሐሳብ የበላይ ሲሆን የጦር መሣሪያ የእርሻ መሣሪያ ወደ መሆን ይለወጣል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቴሌቪዥን መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ስለሆነች ልንጠብቃት፣ አለመግባባታችንንም በውይይት ልንፈታ፣ ቃላችንን ደግሞ መሬት ላይ አሳርፈን እርቁን እውነተኛ ልናደርግ ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ለተደረሰው ስምምነት የደከሙትን እና ጥሪውን የተቀበሉትን አመስግነዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!