አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማቋቋም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት÷ የክልሉ መንግስትና ህዝብ የሰላም ስምምነቱ በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆን በሙሉ ልብ ከመደገፍ ባሻገር በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመጠገን በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ ነው።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሲካሄድ የነበረውን ጦርነትና ግጭት የሚያስቆም ስምምነት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ህገ መንግስቱን ባስጠበቀ መልኩ መፈጸሙ ታሪካዊ ክስተት መሆኑንም አውስተዋል፡፡
ከሰላም የሚበልጥ ጉዳይ ባለመኖሩ ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ መደረሱ ትልቅ ድል መሆኑን መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የሰላም ስምምነቱ በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል እና መንግስትና ህዝብ ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት እንዲያዞር እድል የሚፈጥር መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
ግጭትና ጦርነት ማቆምና ሰላምን እውን ማድረግ ከመነሻውም የመንግስት ፍላጎት የነበረና ከግጭትና ጦርነት ምንም ትርፍ የማይገኝና አውዳሚ በመሆኑ እዚህ ስምምነት ላይ መደረሱ መላው ኢትዮጵያውያን እንዳስደሰተ ተናግረዋል።
ስምምነቱ የሀገሪቱን ሰላም እና የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ እውን እንዲሆን የማይፈልጉ አካላትን አንገት ያስደፋ መሆኑንን ገልፀው የሰላም ስምምነቱ የተደረሰባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ እንዲሆኑ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡