ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሞዛምቢክ የተፈጥሮ ጋዟን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ብሪታኒያ ላከች

By Alemayehu Geremew

November 14, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሞዛምቢክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ብሪታኒያ ላከች፡፡

ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ ሞዛምቢክን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ የሚገኙት ፊሊፔ ናዩሲ ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ ÷ “ዛሬ ሞዛምቢክ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ ከሚልኩ ሀገራት አንዷ በመሆን በዓለም ታሪክ ትመዘገባለች” ማለታቸውን አር ቲ አጃንስን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡

የሞዛምቢክ የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያ “ኤኒ” በተሠኘ የጣሊያን ኩባንያ የሚመራ ሲሆን የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ጥያቄው የቀረበው ደግሞ ከብሪታኒያ መሆኑ ነው የተጠቆመው፡፡

ሞዛምቢክ ከሰሃራ በረሃ በስተደቡብ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እንዳላት ይነገራል፡፡

በሞዛምቢክ በተጠቀሰው ቦታ 2 ነጥብ 8 ትሪሊየን ኪዩቢክ ሜትር ወይም ከዓለም አጠቃላይ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት 1 በመቶ ገደማውን ያህል እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

በሞዛምቢክ መኖሩ በተረጋገጠው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ሀገሪቷ ከዓለም 10 ቀዳሚ የተፈጥሮ ጋዝ አምራች እና ላኪዎች ተርታ እንድትሠለፍ የሚያስችላት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአፍሪካ ደረጃም ከአልጄሪያ እና ናይጄሪያ ቀጥሎ ሞዛምቢክ በ3ኛ ደረጃ የምትቀመጥ የነዳጅ ላኪ ሀገር እንደምትሆንም ተገልጿል፡፡