የሀገር ውስጥ ዜና

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 200 የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ድጋፍ ተደረገ

By Tamrat Bishaw

November 16, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር 200 የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን ለአዲስ አበባ ከተማ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት÷ የድጋፉ ዓላማ በከተማዋ የተጀመረው የከተማ ግብርና እያሳየ ያለው መነቃቃት በበጋው ወቅትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው፡፡

በድጋፍ መልክ የተበረከቱት ፓምፖችም÷ በመዲናዋ በክረምት የተጀመረው የከተማ ግብርና ቀጣይነት እንዲኖረው ውሃ ባለበት አካባቢ ሁሉ መሳብ የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው÷ ለከተማዋ አቅም ከሆኑ ተቋማት መካከል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በድጋፍ መልክ የተበረከቱት የውሀ መሳቢያ ፓምፖችም÷ በከተማዋ እየተሠራ ያለው ግብርና የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ያግዛሉ ብለዋል።

እነደዚህ ያለው ትብብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋጥ እንደሚረዳ ጠቁመው÷ የውሃ መሳቢያ ፓምፖቹን ለሚመለከተው አካል እንደሚያስረክቡም ተናግረዋል።

በቅድስት ብርሃኑ