አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሶስት አስርት ዓመታት ስራ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ኢነርጂ ፖሊሲ ሊሻሻል መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ በተሻሻለው የኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት÷ ለ29 ዓመታት ስራ ላይ የነበረው የኢነርጂ ፖሊሲ ከ2013 ዓም ጀምሮ የማሻሻያ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቷል።
ፖሊሲው አሁን ካለው ሀገራዊ አሁናዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ ተሻሽሎ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ዓለምን እየፈተነ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ የተጣጣመ ኢኮኖሚን ለማጎልበት እንደሚያግዝ፣ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ኢትዮጵያን በፖሊሲ አቅጣጫ የምትመራበት እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
ከረቂቅ ፖሊሲው ዝግጅቶች በኋላ በርካታ ውይይቶች ተደርገው ወደ መጨረሻ ደረጃ መሸጋገሩን ገልፀው÷ ተጨማሪ ግብዓቶች ከተሰበሰቡ በኋላ ወደ ሚመለከተው አካል ቀርቦ እንዲፀድቅና ስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ነው ያሉት።
የኢነርጂ ፖሊሲው ማሻሻል ምክንያቶች መካከልም ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ፣ ከአረንጓዴ ልማት፣ ከ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድና ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር ማጣጣም በማስፈለጉ ነው ተብሏል።
በቀጣናው የኢነርጂ አቅምን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግም አንዱ የረቂቅ ፖሊሲው ግብ ነው መባሉንም ኢዜአ ዘግቧል።