የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ደመቀ መኮንን መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት ቁርጠኛ መሆኑን ገለጹ

By Shambel Mihret

November 17, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር ጋር ተወያዩ።

ውይይታቸው በሰላም ስምምነቱ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

በውይይቱ ወቅትም አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መንግስት የሰሜኑን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ካለው ፍላጎት መነሻነት የሰላም ስምምነት እንዲደረስ በትኩረት ሲሰራ እንደነበር አስታውሰው ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ግጭት ተፈጥሮባቸው በነበሩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወገኖች የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማስጀመሩ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ፖለቲካዊ ውይይት እንደሚያደርግ በማንሳት በብሄራዊ ምክክር መድረክ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይቶች እንደሚካሄዱም ነው የገለጹት፡፡

የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበው፥ በቀጣይ በስምምነቱ ትግበራ ምዕራፍ እና መልሶ ማቋቋሙ ላይ አጋር አካላት ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ልዩ መልክተኛዋ በበኩላቸው የተደረሰው ስምምነት ታሪካዊ መሆኑን በመጥቀስ፥ የአውሮፓ ህብረት ለስምምነቱ ተግባራዊነት እና መልሶ ማቋቋም የድርሻውን ሚና ይወጣል ብለዋል፡፡