የሀገር ውስጥ ዜና

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከጀርመን ፌደራል ፖሊስ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ

By Feven Bishaw

November 17, 2022

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የጀርመን ፌደራል ፖሊስ ተወካይና የፖሊስ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ አማካሪ በሆኑት ሚስተር ሄለም ሽሮት ከተመራው ልዑካን ቡድን መክረዋል፡፡

በውይይቱ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፥ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ ስኬታማ ተግባራት እና ተቋሙ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ ለልዑካን ቡድኑ አስረድተው የታጠቃቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችም ተዘዋውረው እንዲጎበኙ አድርገዋል።

የጀርመን ፌደራል ፖሊስ ተወካይና የፖሊስ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ አማካሪ ሄለም ሽሮት በበኩላቸው÷በአፍሪፖል ዲዛይን የተደረጉ ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር ከፍተኛ እገዛ የሚያደርገውን የሰነድ ምርመራ ላይ የጀርመን ፌደራል ፖሊስ ዝግጁ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ሰንቆ የተነሳውን ራዕይ ለማሳካት እያደረገ ያለውን ብርቱ ጥረት እንደሚደግፉ መናገራቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

እንዲሁም ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በፀጥታና ደህንነት ዘርፍ በጋራ በሚያሰሩ ጉዳዮች ዙሪያ ግንኙነታቸውን የበለጠ በማጠናከር እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

አያይዘውም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ፎረንሲክ ዲፓርትመንትን ለማዘመን እየተደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት በሥልጠና እና በሎጂስቲክ ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።