አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተቋማት ትስስርና ቅንጅታዊ አሠራር ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ወሳኝነት መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትየጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ያለበትን ደረጃ ለመገምገም፣ ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠናከርና የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
አቶ መላኩ አለበል በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ አዳዲስ ኢንቨትመንት በመሳብ፣ የመሰረተ ልማትና የመሬት ጥያቄዎችን በመመለስ እንዲሁም ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከፌደራል እስከ ክልልና ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሠራር መዘርጋት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት፣ የዜጎችን ገቢ ማሳደግ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እና ተወዳዳሪነትን ከፍ ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡
አዳዲስ አሠራሮችን፣ ሐሳቦችንና አካሄዶችን ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ የኢትየጵያን ህዳሴና ብልጽግና ማረጋገጥ እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ አጠቃላይ ገጽታ የሚያሳይ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት የኢዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በውይይቱ የፌደራል፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡