አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የባለሦስት እግር ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች ማኅበራት መሪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሔደ፡፡
የውይይቱ ዓላማ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥና በሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ትርፍ መጫን፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣በህግ ከተቀመጠው የተሽከርካሪዎች የመንጃ ፈቃድ ውጭ በመጠቀም ማሽከርከር፣ ከተፈቀደላቸው የስምሪት መስመር ውጭ መሰማራት፣ የስምሪት መስመርን ማቆራረጥ የሚሉ ችግሮች መኖራቸው ለውይይት በቀረበው ሰነድ ላይ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በኮንትራት አገልግሎት ስራ በይበልጥ ደግሞ ምሽት ሰዓት ላይ ህገወጥ ተግባራትን መስራትና መተባበር፣ የአሽከርካሪዎች የአቅም ማነስ መኖር፣ለስምሪት አካላት ታዛዥ አለመሆን፣ህግን አክብሮ ለአገልግሎት ፈላጊው ማህበረሰብ አለማገልገል የሚሉ ችግሮች አንዳሉ ተመላክቷል፡፡
ከመድረኩ መሪዎች በተሰጠ ምላሽ እና ማብራሪያ÷ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡
ችግሩን ለማቃለልም የህግና የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት በዘላቂነት በመቀናጀት ለመፍታት ከዚህ በኃላ ተደጋጋሚ የምክክር መድረኮች እንደሚፈጠሩ ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም ሕብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ህገ ወጥነትን በማጋለጥ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡