አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የሌማት ትሩፋት ማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ተካሄደ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የተመጣጠነ ስርአተ ምግብን እውን ለማድረግ፣ የምግብ ሸቀጥ ምርቶችን ዋጋ ለማረጋጋትና ከውጭ የሚገቡትን ለመተካት እንዲሁም የሥራ እድልን ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
መርሐግብሩ በከተማና በገጠር እንደሚተገበር ጠቁመው÷ መርሐ ግብሩ የሕዝቡና የመንግሥት የርብርብ ማዕከል መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት በዘርፉ ለተሠማሩ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርም አረጋግጠዋል፡፡
ጠንክረን ከሠራንና ያሉንን ፀጋዎች አሟጠን ከተጠቀምን÷ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ እና በአቮካዶ ምርቶች ያስመዘገብነውን ውጤት በስጋ፣ በወተት፣ በዶሮ፣ በእንቁላል እና በማር ማሳካት እንችላለን ብለዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሚስራ አብደላ እንደገለጹት ከሌማት ትረፋት ጋር በተያያዘ÷ ንብ ማነብ፣ የስጋና ወተት ከብቶች እንዲሁም የዶሮና ዓሣ እርባታ ሥራዎች ይተገበራሉ፡፡
መርሐ ግብሩ እውን እንዲሆን የመሬት እና ቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ የዝርያ ማሻሻል እንዲሁም የገበያ ትስስር በመፍጠር ለአምራቹም ሆነ ለሸማቹ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ከመርሐ ግብሩ ማስተዋወቂያ በኋላ በእንስሳት እርባታ የተሰማሩ ግለሰቦች የሥራ እንቅስቃሴ ተጎብኝቷል፡፡
በተሾመ ኃይሉ