አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የሙስና ወንጀልን ለመከላከል እና የወንጀሉን ተዋንያን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ክልላዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
ኮሚቴው በተለያዩ መዋቅሮች በተደራጀ መልኩ የሚፈፀም የመሬት ነክ ሙስና፣ ከግብር፣ ከግዥ፣ ለፕሮጀክቶች፣ ከግንባታ ፍቃድ፣ ከመንጃ ፍቃድ ህገ ወጥ ንግድ የሚፈፀም ሙስናን በመከላከል ወንጀለኞች ለህግ ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
እንዲሁም ከኢንቨስትመንት፣ ለመንግስታዊ አገልግሎቶች ከዜጎች የሚጠየቅ ጉቦ፣ በፍትሕ ዘርፍ እና በሌሎችም ዘርፎች የሚፈፀም ሙስናን በመከላከል ወንጀለኞች ለህግ ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የተቋቋመውና አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴው በሙስና ወንጀል ላይ የሚያደርገውን የህግ ማስከበር ዘመቻ የሚያስተባብር፣ የወንጀሉን ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ነው።
ይህ የፀረ ሙስና ክልላዊ ኮሚቴ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት እንዲችል የህብረተሰቡ ሙሉ ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ የሙስና ተዋንያንን በተመለከተ ያለውን መረጃ በቀጣይ ቀናት በክልላዊ ኮሚቴው ለህዝብ ይፋ በሚያደርጋቸው አድራሻዎች በመላክ ሙስናን ለማጥፋት በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል፡፡