የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ፣ በአህጉራችን አፍሪካ፣ እንዲሁም በሃገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት የደቀነ ወረርሽኝ ነው። በአሁኑ ወቅት ይህን ወረርሽኝ መግታት እና መከላከል ትልቅ ሃገራዊ የትኩረት አጀንዳ ነው። የዜጎችን ህይወት እና ጤና፤ የሃገርን ህልውና እና ደህንነት አደጋ ላይ የጣለውን የዚህን ወረርሽኝ ስርጭት ለመመከት የሁላችንም ጥረት እና ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው።
እስካሁን በተለያዩ ሃገራት የተከሰተውን የወረርሽኙን ስርጭት፣ እንዲሁም የአለም ጤና ድርጅት እና የሃገራችን የጤና ባለሞያዎች እና ተቋማት የሚያቀርቡዋቸውን ሞያዊ መረጃዎች እና ምክሮች ከግምት በማስገባት መንግስት ወረርሽኙን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወቃል። ህዝቡ ስለበሽታው መረጃ ኖሮት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዲችል ስለወረርሽኙ ባህሪያት እና መተላለፊያ መንገዶች በየጊዜው ከሚሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የጥንቃቄ እርምጃዎች በየደረጃው እንዲወሰዱ መንግስት ውሳኔ ማስተላለፉ እና መመሪያዎች መሰጠታቸው ይታወሳል።