አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከ17 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ማመንጨት መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ፡፡
የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ጥሩወርቅ ሽፈራው እንደገለጹት ÷ከጥቅምት 1 ጀምሮ ወደ ኦፕሬሽን ከገቡ 16 የንፋስ ተርባይኖች 17 ጌጋ ዋት ሠዓት ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ 17 ነጥብ 7 ጌጋ ዋት በሰዓት በማመንጨት መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
ተርባይኖቹ ከዕቅድ በላይ ማመንጨታቸው በአካባቢው ያለው የንፋስ ኃይል ፍጥነት ከፍተኛ መሆኑ በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የፍተሻ ሥራ ላይ በነበረበት መስከረም ወር ላይ 3 ነጥብ 3 ጌጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ወደ ኦፕሬሽን በገቡ የንፋስ ተርባይኖች የመነጨው ኃይል፤ ከሌሎች መሰል ጣቢያዎች የተሻለ ኃይል ማምረት እንደሚቻል ያሳየ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ከንፋስ የሚገኘውን የኃይል ምንጭ ለማሳደግ በአይሻ 2 አካባቢ ያለው አማካኝ የንፋስ ፍጥነት ተስፋ የሚሰጥ ነው ሲሉ ስራ አስኪያጇ መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ሀይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡