ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቱርክ 12 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ አዲስ የነዳጅ ክምችት አገኘሁ አለች

By Alemayehu Geremew

December 13, 2022

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱርክ 12 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ አዲስ የነዳጅ ዘይት ክምችት ማግኘቷን አስታወቀች፡፡

ቱርክ በደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቷ ክፍል በምትገኘው ሲርናክ ግዛት ጋባር ተራራ ላይ ያገኘችው የነዳጅ ክምችት ከተጣራ በኋላ 150 ሚሊየን በርሜል እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶኻን በጉዳዩ ላይ ከሚኒስትሮቻቸው ጋር ከመከሩ በኋላ ነው መረጃውን ይፋ ያደረጉት ተብሏል፡፡

ከአራት የነዳጅ ጉድጓዶች ውስጥም በቀን 5 ሺህ በርሜል ከፍተኛ ጥራት ያለው ነዳጅ እንደሚወጣ ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን ለአናዱሉ መግለጻቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የበርካታ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ አውጪ ኩባንያዎች ሥራ ተቀዛቅዞ በነበረበት የፈረንጆቹ 2021 ቱርክ 34 ያህል የነዳጅ ፍለጋ አሰሳ አካሂዳለች፡፡

ባገኘችው ውጤትም አሁን ባለው ሀገራዊ የነዳጅ ክምችት መጠኗ ላይ ተጨማሪ 71 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ መጨመሯን አስታውቃለች፡፡

በፈረንጆቹ 2022 ከተካሄዱ 10 ትላልቅ የነዳጅ አሰሳዎች እና ግኝቶች ውስጥ አዲሱ የቱርክ የነዳጅ ግኝት አንዱ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡