አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ የመረጃ መኮንኖች በሰላም እና በፀጥታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት በካርቱም ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ መከላከያ መረጃ ዋና ምመሪያ ሜጄር ጄኔራል ደምሰዉ አመኑ፥ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ዘመናትን የተሻገረ ባህል እና ታሪክን የሚጋሩ ህዝቦች ናቸው ብለዋል፡፡
ይህ የመቻቻል እና የአብሮነት መልካም አሻራ በዘላቂነት እንዲቀጥል በጋራ እና በትብብር በሰላም እና በፀጥታ ዙሪያ መስራቱ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የሱዳን ወታደራዊ መረጃ ሃላፊ ሜጄር ጄኔራል መሃመድ ዓሊ አህመድ በበኩላቸው÷በጋራ የመስራት ስምምነትቱ ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ ወታደራዊ የመረጃ መኮንኖች በሀገራቱ የመረጃ ተቋማት መካከል ሊሰሩ በሚገባቸው የሰላም እና የፀጥታ እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ ስራዎች ላይ መክረዋል፡፡
በመድረኩ የሱዳን መከላከያ ምክትል ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጄኔራል መጅዲ ኢብራሂም ኡስማን፣ በሱዳን የኢትዮጵያ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል አብደላ መሃመድ እና ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች መገኘታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡