የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ለበዓሉ የመብራት መቆራረጥና የውሃ ችግር እንዳያጋጥም የተቀናጀ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል

By Alemayehu Geremew

January 04, 2023

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በበዓል የመብራት መቆራረጥና የውሃ ችግር እንዳያጋጥም የተቀናጀ ግብረ- ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን የከተማ አስተዳደሩ ሥራ አስኪያጅ ጽኅፈት ቤት ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ጽኅፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ በሰጡት መግለጫ ÷ የፊታችን ቅዳሜ ለሚከበረው የገና በዓል የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሳለጠ አገልግሎት ለነዋሪው ለማቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይም የመብራት መቆራረጥና የውሃ ችግር እንዳያጋጥም ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው ÷ የተቀናጀ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን አመክተዋል፡፡

የእነዚህ አገልግሎቶች ችግር ቢያጋጥምም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

ሕብረተሰቡ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበው ÷ አደጋ ቢያጋጥም እንኳን የእሳትና ድንገተኛ አደጋ በዋናው መሥሪያ ቤቱና በዘጠኙም ቅርንጫፎቹ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅትም ለበዓሉ ጤናማ የሆነ ሥጋ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት፡፡