አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ የሚገኙትንና ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ የውሃ ሀብቶችን በብቃት መጠበቅና መጠቀም ለሀገሪቱ ሕዝቦች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በውሃ ሀብት ላይ ምርምር የሚያደርጉ ምሁራንና የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
”ሀገራዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ከብሔራዊ ደኅንነት አንጻር” በሚል መሪ ቃል በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አዘጋጅነት የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ በቁጥር እየጨመረ የመጣውን የሕዝቧን ፍሏጎት ለሟሟላት በውስጧ የያዘችውን የውሃ ሀብትና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿን ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በሚገባ መጠቀም ይኖርባታል።
ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን የፍትሃዊነትና ምክንያታዊነት መርህን በመከተልና በማረጋገጥ የምትጠቀም ሀገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋዎች የሆኑት በድንበሯ ውስጥ ያሉትና ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች ከሀገር ህልውና ጋር የተሳሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህም ወጥ የሆነ የውሃ ፖሊሲና ስትራቴጂ መዘርጋትና ሥራ ላይ ማዋል እንዲሁም በውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲዎች ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የውሃ አጀንዳ ከብሔራዊ ደኅንነትና ህልውና ጉዳይ ጋር የተያያዘ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሀገራዊ ጉዳይ በመሆኑ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማትን ጨምሮ የሚመለከታቸው የዘርፉ መሥሪያ ቤቶች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎችና ምሁራን እንዲሁም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን ግንዛቤና እውቀት እንዲጨብጡ የሚያስችሉ መድረኮችን ማስፋፋትና ተቋማዊ አቅምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም አቶ ታዜር አያይዘው ገልጸዋል።
ከውሃ ሀብቶች ጋር የተያያዙ እውቀቶች እንዲያድጉ የስርዓት ትምህርቱ አካል ማድረግ ጠቃሚ ነው የሚል ሐሳብም መሰንዘሩንና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያግዙ ሥራዎች ያስፈልጋሉ የሚል አስተያየትም በተሳታፊዎች መንጸባረቃቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ አመልክቷል።