የሀገር ውስጥ ዜና

ከዋግኽምራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከበዓል በፊት የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሠራጭ እየተሠራ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

January 05, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዋግኽምራ ዞን አበርገሌ ወረዳ ለተፈናቀሉ 31 ሺህ 839 ወገኖች ከገና በዓል ቀድሞ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማሠራጨት እየሠራ መሆኑን ኤፍ ኤች ኢትዮጵያ አስታወቀ፡፡

በኤፍ ኤች ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፕሮግራም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ዳንኤል ጥላሁን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ቅድሚያ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቅለው 31 ሺህ 839 የአበርገሌ ወገኖች ከገና በዓል ቀድሞ የሰብዓዊ ድጋፍ ይሰራጫል፡፡

ለዚህም 5 ሺህ 396 ኩንታል ከኮምቦልቻ ወደ ሰቆጣ ከትናንት ጀምሮ እየተጓጓዘ መሆኑን ጠቁመው÷ የማከፋፈያ ሠነዶችና ባለሙያዎች ዝግጁ በመሆናቸው ከስርስር የሚደርሰው ድጋፍ ይሰራጫል ነው ያሉት፡፡

እስካሁንም 45 በመቶ ያህሉ ወደ ሰቆጣ መላኩን አቶ ዳንኤል አረጋግጠዋል፡፡

ኤፍ ኤች ኢትዮጵያ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የከፋ የምግብ ክፍተት ባለባቸው ፥ አበርገሌ፣ ዝቋላ እና ሳኅላ ወረዳዎች ላይ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በድርጅቱ ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙት የአበርገሌ ተፈናቃዮች ቁጥር 37 ሺህ 960 መሆኑን እና 6 ሺህ 121 ያህሉ የአበርገሌ ተፈናቃዮች በሳኅላ ወረዳ በኩል ድጋፉ ተደራሽ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፥ ለአበርገሌ ተፈናቃዮች ተሰራጭቶ ሲጠናቀቅ ለዝቋላ እና ሳኅላ ወረዳዎች ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምግብ እህል ይጓጓዛል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!