አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 ዓ.ም ግማሽ ዓመት በአማራ ክልል 2 ሺህ 575 አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱት አልሚዎች ከ144 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸው ተገልጿል፡፡
በቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይኸነው ዓለም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በተጠናቀቀው ስድት ወር ከ144 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 2 ሺህ 575 አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል፡፡
ፈቃድ የወሰዱት አልሚዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ577 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል፡፡
አብዛኞቹ መንግሥት በልዩ ሁኔታ በሚያበረታታቸው ዘርፎች ማለትም በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በብረታብረት፣ በእንጨት፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ፈቃድ መውሰዳቸውን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም በአገልግሎት ዘርፍ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በግብርናና በአበባ ልማት ዘርፎች ፈቃድ የወሰዱ መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ምንም እንኳን የውጭ ሀገር አልሚዎች ፍሰት መቀነስ ቢያሳይም÷ መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽና ፈጣን ለማድረግ እንዲሁም አልሚዎችን ለመደገፍ ባሳየው ቁርጠኝነት የሀገር ውስጥ አልሚዎች ፍሰት መጨመሩን ነው የተናገሩት፡፡
የክልሉ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ አልሚዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ያሉት አቶ ይኸነው÷ በባሕር ዳር እና ቡሬ ከተሞች ለአልሚዎች የተዘጋጁ ሸዶች፣ መሰረተ ልማት የተሟላለት እና ያልተሟላለት መሬት መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል፡፡
በሌሎች የክልሉ ከተሞችም ለአልሚዎች መሬት መዘጋጀቱን ጠቁመው ባለሀብቶች በክልሉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም 175 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ እና ከ506 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያላቸው 2 ሺህ 782 አልሚዎች ፈቃድ መውሰዳቸውን አስታውሰዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!