አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ሥድስት ድልድዮች ተገቢው ጥገና ተደርጎላቸው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድልድይ እና ስትራክቸር ሥራዎች ዳይሬክተር ጌትነት ዘለቀ ፥ የአልውሃን ድልድይ ጨምሮ ለሥድስት ድልድዮች በ175 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የጥገና ስራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
የአልውሃ ድልድይ ከዚህ ቀደም ጉዳት ደርሶበት የነበረ ሲሆን ፥ በወቅቱ 54 ነጥብ 86 ሜትር ርዝመት ያለው የብረት ድልድይ ተሰርቶለት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ሆኖም ግን ድልድዩ ዳግመኛ በመጎዳቱ ምክንያት በጊዜያዊነት በተሠራው የብረት ድልድይ ላይ የመውደቅ ስጋት በማስከተሉ 109 ነጥብ 73 ሜትር ርዝመት ያለው አዲስ የብረት ድልድይ ሊገነባ ስለመቻሉም ነው የተገለጸው።
በዚህም ከወልዲያ ወደ ቆቦ ከሚያሻግረው የአልወሃ ድልድይ ባሻገር፣ ከሚሌ-ጭፍራ-ወልዲያ የሚያሻግረው 48 ነጥብ 86 ሜትር የሚረዝመው የጨረቲ ድልድይ ፣ ሁመራ እና ሽሬን የሚያገናኘው 27 ነጥብ 43 ሜትር የተከዜ 3 ድልድይ ፣ ከቆቦ የገጠር አካባቢዎች ጋር የሚያገናኘው 48 ነጥብ 86 ሜትር የጎቡ ድልድይ ተገቢው ጥገና ተደርጎላቸው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
በተጨማሪም ከአምደወርቅ ወደ እብናት በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው 48 ነጥብ 86 ሜትር የተከዜ ድልድይ እና ከኮረም ወደ ሰቆጣ የሚወስደው 42 ነጥብ 67 ሜትር የጽላሬ ድልድዮች ተገቢው ጥገና ተደርጎላቸው አገልግሎት እየሰጡ ነው ተብሏል።
በቀጣይም በእነዚህ አካባቢዎች ጉዳት በደረሰባቸው ድልድይና መንገዶች ላይ አስፈላጊ የጥገና ብሎም የደረጃ ማሻሻል እና የማሳደግ ተግባራት እንደሚከናወን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡