የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በቅንጅት እየተሰራ ነው

By Amele Demsew

January 28, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግጭቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ተፈሪ ታረቀኝ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በክልሉ ግጭት በነበረባቸው ስምንት ዞኖች በሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ከ18 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ውድመት ደርሷል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎቹ የደረሰባቸው ጉዳት መጠን በጥናት መለየቱን የተናገሩት ሃላፊው፥ እስካሁን 141 የሚሆኑ ተቋማት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ስራ አለመግባታቸውን አንስተዋል፡፡

በግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን አምራች ኢንተርፕራይዞችን መልሶ ለማቋቋም ከፌዴራል መንግስት በተለየ መልኩ የሚደረገው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑንም አስረድተዋል ፡፡

በአንጻሩ ጉዳት ከደረሰባቸው አምራች ኢንተርፕራይዞች ውስጥ አብዛኞቹ ወደ ስራ መግባታቸውን ነው ሃላፊው የጠቆሙት፡፡

በቀጣይ ተቋማቱ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከአትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በአማራ ክልል አሁን ላይ ከ2 ሺህ 400 በላይ የሚሆኑ አዳዲስ አምራች ኢንተርፕራይዞች በግንባታ ሒደት ላይ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል 3 ሺህ 422 በላይ ከፍተኛ ፣ መካከላኛ እና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርት በማምረት ሂደት ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

በመላኩ ገድፍ