የሀገር ውስጥ ዜና

በሲዳማ ክልል 416 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚሰራ ተገለጸ

By Shambel Mihret

January 31, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ416 ሺህ ሄክተር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚሰራ የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው በዳራ ኦቲልቾ ወረዳ ሌላወመሬራ ቀበሌ የተጀመረ ሲሆን ፥ ክልሉ ለአንድ ወር በሚቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ 558 ንዑስ ተፋሰሶችን ለማልማት ማቀዱ ተነግሯል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አበራ ዊላ እንደገለጹት ÷ በዚህ የአፈርና ወሃ ጥበቃ ላይ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰው ይሳተፋል፡፡

ይህም ለግብርናው እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቅሰው ÷ ክልሉ ተራራማ አካባቢ የሚበዛበት በመሆኑ አፈር በዝናብ እየተሸረሸረ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን አርሶ አደሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ መስራት በመጀመሩ ለውጦች እየታዩ መሆኑን ያነሱት ምክትል ሃላፊው ÷ እርከንን ጨምሮ ሌሎች የአፈርና ወሃ ጥበቃ ስራዎች ይከወናሉ ነው ያሉት፡፡

መንግስት የአርሶ አደሩን ህይወት ለመደገፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና አርሶ አደሩም በጉልበቱ መስራት የሚችለውን ነገር ሳይደክም መስራት አለበት ብለዋል፡፡

ክልሉ የመስራት አቅሙን ከተጠቀመ ሁሉንም ምርት ማግኘት እንደሚቻል የገለጹት ደግሞ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ  ፅ/ቤት ምክትል ሃላፊና የፖለቲካና ርዕዮተ- ዓለም ዘርፍ ሃላፊ አስፋው ቦኔሳ ናቸው፡፡

በጥላሁን ይልማ