የሀገር ውስጥ ዜና

የአካል ጉዳተኞች እኩል እድልና ሙሉ ተሳታፊነት እንዲረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By Amele Demsew

January 31, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአካል ጉዳተኞች እኩል እድልና ሙሉ ሳታፊነት እንዲረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

አለም አቀፍ የስጋ ደዌ ቀን በኢትዮጵያ ለ24ኛ ጊዜ ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ69ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትር አማካሪ አቶ ጌታቸው በዳኔ ጉዳዩን አስመልክቶ እንደተናገሩት ፥ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ተገቢውን ምላሽ መስጠት ግድ ይላል ፡፡

ሚኒስቴሩ ለማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ችግሮች የተጋለጡ ዜጎች እንዲቋቋሙና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለይም የአካል ጉዳተኞች የእኩል እድልና ሙሉ ተሳታፊነት እንዲረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በጊዜያዊነት ድጋፍ ላይ ብቻ ያልተመሰረተ ዘላቂነት ያለው የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን የመገንባት ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማንሳታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ሀና የሺንጉስ በበኩላቸው ÷ የበዓሉ ዓላማ በስጋ ደዌ ተጠቂዎች ላይ የሚደርሰውን ማገለልና መድሎ ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ የሚያስችሉ ስራዎችን በስፋት ለመስራት ነው ብለዋል፡፡

የስጋ ደዌ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ደረጃ 2 የአካል ጉዳት የተገኘባቸው አዳዲስ የስጋ ደዌ ህሙማን መጠን ከ5 በመቶ በታች ለማድረስ እየተሰራ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡