የሀገር ውስጥ ዜና

ዓለም አቀፉ ግብረ ሠናይ ድርጅት በኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ለሚገኙ ሴት ተፈናቃዮች የሚውል የ1 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አገኘ

By Alemayehu Geremew

February 01, 2023

አዲስ አበባ ፣ ጥር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “አክሲየን” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ግብረ-ሠናይ ድርጅት በኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ለሚገኙ ሴት ሥደተኞች ድጋፍ የሚያውለው 1 ሚሊየን ዶላር ከኮናርድ ሂልተን ፋውንዴሽን ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ግብረ-ሠናይ ድርጅቱ ÷ ሥደተኞቹ በሚገኙበት ሀገር ከሚሠሩ የፋይናንስ ፣ የንግድ እና የማኅበረሰብ ተቋማት ጋር በመተባበር ሥራ መጀመር የሚያስችላቸውን መነሻ ገንዘብ እና ሥልጠና እንደሚያመቻች ዛሬ በገፁ ባወጣው መረጃ አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ እና በኡጋንዳ ገጠራማ የሀገራቱ ክፍሎች ከመሠረታዊ አገልግሎቶች የተገለሉ ከ 2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሥደተኞች መሥፈራቸውንም ነው የጠቆመው፡፡

የአሲየን ግብረ-ሠናይ ድርጅት ፕሬዚዳንት እና ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ሚካዔል ሽላይን ÷ ሴት ሥደተኞቹ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ ከሂልተን ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር እንሠራለን ብለዋል፡፡

በሚኖሩበት ማኅበረ-ሰብ ውስጥ በአነስተኛ ንግዶች ላይ ተሠማርተው በኢኮኖሚ ጠንካራ የሚሆኑበት መንገድ እንዲፈጠር እና ከራሳቸው አልፈው አካባቢያቸውን በኢኮኖሚ እንዲገነቡ ብድር እንደሚያቀርቡም ተመልክቷል፡፡