አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የጣልያን ግንኙነት ለብዙ ዘመናት የቆየ እና ፍሬያማ የሆነ አጋርነት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ጣልያን ሮም መግባታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ “ዛሬ ጠዋት በፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ለተደረገልን አቀባበል ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን እና የጣልያንን ግንኙነትም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሚኒስትሮች ልዑክ ቡድን በሮም ጣሊያን የሥራ ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡
ከጉብኝቱ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት÷ በኢትዮጵያ እና ጣልያን መካከል ስላለው ግንኙነት መክረዋል፡፡
በተጨማሪም በሌሎች ወቅታዊ፣ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡