የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል በግጭት ምክንያት ውኃ ለተቋረጠባቸው 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ወገኖች በድጋሚ ማቅረብ ተቻለ

By ዮሐንስ ደርበው

February 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግጭት ምክንያት የውኃ አቅርቦት ተቋርጦባቸው ለነበሩ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ወገኖች በድጋሚ ማቅረብ መቻሉን የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ከ20 በላይ ግብረ ሠናይ ድርጅቶችን በማቀናጀት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ፈንድ በማፈላለግ ነው አገልግሎቱን በድጋሚ ማቅረብ የቻለው፡፡

በአንጻሩ አሁንም በክልሉ በግጭት ምክንያት በወደሙ መሰረተ ልማቶች ምክንያት ከ4 ሚሊየን በላይ ወገኖች የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እንደተቋረጠባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

አቅመ ደካሞች፣ ሕጻናት፣ ሕሙማን በአቅራቢያቸው ውኃ እንዲገኙ፥ መንግሥት፣ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች፣ ዳያስፖራዎች፣ ባለሃብቶች እና ሕብረተሰቡ ርብርብ እንዲያደርጉ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል፡፡

የወደሙ የውኃ ተቋማትን በተሻለ ቴክኖሎጂ በመገንባት እና በመጠገን ሕዝቡን መካስ እንደሚገባ በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወንዳጥር መኮንን ተናግረዋል፡፡

በአንዳንድ ወረዳዎች ላይ ሕብረተሰቡ ቀለል ያሉ ጥገናዎችን በራሱ ኃይል ጠግኖ በድጋሚ አገልግሎቱን በማስጀመሩ ቢሮው ምስጋና እያቀረበ ይህ ተነሳሽነት እንዲጠናከር ጠይቋል፡፡

በድጋሚ አገልግሎቱን ለማስጀመር የኤሌክትሮ መካኒካል ዕቃዎች፣ ጄኔሬተሮች፣ ፓምፖች እና ተሽከርካሪዎች ግዥ በቀጥታ በሀገር ውስጥ አለመገኘት እንደፈተናቸውም ነው አቶ ወንዳጥር ያመላከቱት፡፡

በክልሉ በተወሰኑ ዞኖች በነበረው ግጭት ምክንያት ከ1 ሺህ 429 በላይ የውኃ ተቋማት መውደማቸው እና በዚህም ከ2 ነጥብ 64 ቢሊየን ብር በላይ ኪሣራ መድረሱን አስታውሰዋል፡፡

8 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ደግሞ አገልግሎቱ ተቋርጦባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!