የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ2 ነጥብ 494 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

By Amele Demsew

February 06, 2023

አዲስ አበባ ፣ ጥር 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ2 ነጥብ 494 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አባይ መንግስቴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷በክልሉ በተለይም ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ የቱሪዝሙ ዘርፍ መነቃቃት ታይቶበታል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት በሚፈለገው መንገድ ባይሆንም በተገኘው አንፃራዊ ሠላም በመታገዝ ዘርፉን ከወደቀበት በማንሳት፣ በማነቃቃትና በማስተዋወቅ በክልሉ ያሉትን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ በማስቻል በኩል የተቀናጀ ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት፡፡

በዚህም÷በበጀት አመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ 9 ሚሊየን 284 ሺህ 909 የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ፣11 ሺህ 364 የውጭ ጎብኚዎች በድምሩ 9 ሚሊየን 296 ሺህ 273 ጎብኚዎች የክልሉን የቱሪዝም መዳረሻዎች መጎብኘታቸውን ምክትል የቢሮ ሃላፊው አስረድተዋል፡፡

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተሰራ በርካታ ስራ 2 ቢሊየን 494 ሚሊየን 24 ሺህ 800 ብር ገቢ መገኘቱንም ነው የገለጹት ፡፡

በቀጣይ የጎብኚዎችን ቆይታ ለማራዘም የሚያስችል የተቀናጀ ስራ መስራት ፣የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ እና የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እና መሰል ተግባራትን ማከናወን የቢሮው ትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውንም ምክትል የቢሮ ሃላፊው አንስተዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው