የሀገር ውስጥ ዜና

የኮሮና ቫይረስ የወቅቱ ከፍተኛ ችግር በመሆኑ ቀዳሚ ትኩረት ሆኖ መከላከሉ ላይ መሰራት አለበት – የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

By Tibebu Kebede

April 07, 2020

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ በዜጎች ላይ ያንዣበበ የወቅቱ ከፍተኛ ችግር በመሆኑ ቀዳሚ ትኩረት ሆኖ ለመከላከሉ መሰራት እንዳለበት የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት ከሁሉ በላይ የዜጎች ደህንነት የሚቀድም በመሆኑ ለሚሰሩት ስራዎች ድጋፋችን ይቀጥላል ብለዋል።

ምርጫ እና ፖለቲካ እንዲሁም ሌሎችም ዜጎች ሲኖሩ የሚፈጸሙ፤ እውን የሚሆኑ ጉዳዮቻችን አሁን ፋይላቸው ከስር ሆኖ ትብብራችን እና አንድነታችን ቫይረሱን መከላከል በዚህም ሀገራዊም የዜግነትም ግዴታችንን መወጣት ይጠበቅብናል ይላሉ።

የኢዜማ ህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ፥ ፓርቲያቸው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከመጋቢት 7 ጀምሮ የተለያዩ ስብሰባዎች እንዳይደረጉ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን ተናግረዋል።

ኢዜማ እንሰራልሃለን የምንለውን ህዝብ ከሞት መንጋጋ ከማስጣል የሚበልጥ የሚቀድም አንገብጋቢ ጉዳይ ለአሁን የለም ብሏል።

ከዚያም ባለፈ ፓርቲው የመረዳዳት ባህልም በደጋፊዎቹ እና አባላቶቹ መካከል ስር እንዲሰድ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሳልሳዊ ወያኔ ትግራይ ሊቀመንበር ሀያሉ ጎደፋይም፥ ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ዜጎች ራሳቸውን ከዚህ አስከፊ በሽታ እንዲጠብቁ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።

ይህ በሀገር እና የዓለም ዜጎች ላይ የመጣ አስከፊ ነገር ነዉና ከትብብር የተሻለ መፍትሄ የለምም ብለዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ  ትብብር ፓርቲም፥ የፉክክር እና የመሽቀዳደም ፖለቲካዊ ሩጫ ወደ ጎን በመተው አሁን ላይ የጋራ ጠላታችን ላይ የጋራ ክንዳችንን ማሳረፍ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ከዜጎች እና የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቫይረሱን ከመከላከል አንጻር ትልቅ ሀላፊነት ይጠበቃልም ነው ያሉት።

በሌላ መልኩ ደግሞ ከመንግስት ድርብ ኃላፊነት ይጠበቃል የሚሉት የኦነግ ህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ ቀጄላ መርዳሳ፥ ሀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባውም ይመክራሉ።

ይህ የዜጎችን የማይተካ ህይወት ለመንጠቅ ያንዣበበው እስካሁንም በአለም አቀፍ ደረጃ በዙዎች ላይመለስ እስከወዲያኛዉ እንዲያሸልቡ ያደረገዉ ቫይረስ ለመከላከል ልዩ ትኩረት እና ጥረት ስለመፈለጉም አንስተዋል።

ከዚህ አንገብጋቢ የቤት ስራችን በመለስ ሌሎች ነገሮቻችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረን መፍታት ይቻላልም ሲሉ ፖለቲካ ፓርዎቹ ገልጸዋል።

በአፈወርቅ አለሙ