ዓለምአቀፋዊ ዜና

በናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቦላ ቲኑቡ ማሸነፋቸው ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

March 01, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሣምንቱ መጨረሻ በናይጄሪያ የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የገዢው ፓርቲ ዕጩ ቦላ ቲኑቡ አሸናፊነት መጠናቀቁ ተገለጸ።

የሀገሪቷ ገለልተኛ የምርጫ አሥፈጻሚ ኮሚሽን እንዳስታወቀው፥ የቀድሞው የሌጎስ አስተዳዳሪ ቦላ ቲኑቡ 8 ነጥብ 79 ሚሊየን ድምፅ በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል።

ዋና የቲኑቡ ተቀናቃኝ እና ተፎካካሪ የነበሩት አቲኩ አቡበከር ደግሞ 6 ነጥብ 98 ሚሊየን ድምፅ በማግኘት በጠባብ የድምፅ ልዩነት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ሳያሸንፉ መቅረታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡

በናይጄሪያ ወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑት ፒተር ኦቢ 6 ነጥብ 1 ሚሊየን ድምጽ ማግኘታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቴክኖሎጂ ታግዟል የተባለውን የምርጫ ሂደት እና ውጤት አንቀበልም ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡