የሀገር ውስጥ ዜና

ከ33 ሚሊየን ብር በላይ በማሸሽ በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ተከሳሾች ላይ ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ

By Shambel Mihret

March 16, 2023

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጥቁር ገበያን በማስፋፋት ከ33 ሚሊየን ብር በላይ በማሸሽ በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ሶስት ተከሳሾች ላይ ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።

ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች የአዳማ ከተማ ኗሪ እና ነጋዴ የሆኑት 1ኛ አቶ ሀምዛ አሕመድ መሀመድ፣ 2ኛ ተከሳሽ ወይዘሮ ሙንታሃ አብዱራሀም እንዲሁም አቶ ሽፋ መሀመድ ኑር ናቸው።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ዛሬ ከሰዓት በኋላ በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ በንባብ አሰምቷል።

በክሱ ላይ እንደተመላከተው 1ኛ ተከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ተወካይና የትዳር አጋር ሲሆኑ ÷ 3ኛ ተከሳሽ ደግሞ የ1ኛ ተከሳሽ ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን በጋራ ወንጀል መፈጸማቸው ተዘርዝሯል።

ከሰኔ 16 ቀን 2014  ጀምሮ በተለያዬ ጊዜ 1ኛ ተከሳሽ ከጉምሩክ ኮሚሽን ቦሌ ኤርፖርት ቅርጫፍ የተሰጠ በማስመሰል ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን ሰነድ በማዘጋጀት ለ2ኛ ተከሳሽ የሰጡና 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ ከ3ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን ለንግድ ባንክ ሰንጋተራ ቅርጫፍ ሀሰተኛ ሰነዱን ማቅረባቸው በክሱ ተጠቅሷል።

ሀሰተኛ ሰነዱን ለባንኩ ካቀረቡ በኋላ  በ2ኛ ተከሳሽ ስምና በተወካያቸው ስም በሰንጋተራ ቅርንጫፍ በተከፈተ የዳያስፖራ አካውንት የተለያዩ መጠን ያላቸው የአሜሪካ ዶላርና ዩሮ በማስገባት በመመንዘር  33 ሚሊየን 27 ሺህ 465 ብር ወጪ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

ወጪ ካደረጉ በኋላ ገንዘቡን ለግል ጥቅም በማዋል በመንግስትና በህዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በከባድ አታላይነት ሙስና ወንጀል ተከሰዋልም ነው የተባለው።

በሁለተኛው ክስ ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን መገልገል ሙስና ወንጀል እንደተከሰሱም ተጠቅሷል፡፡

በሦስተኛ ክስም ሁሉም ተከሳሾች በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አድርጎ ማቅረብ ሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

ተከሳሾቹ መንግስት የሚቆጣጠረውን የውጭ ምንዛሬ በተጭበረበረ መንገድ  ሕጋዊ ሂደቱን ሳይከተሉ የውጭ ምንዛሬ ሕጋዊ ባለቤት እንደሆኑ በማስመሰል ሕጋዊ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ወደሚደረግበት የባንክ ስርዓት በማስገባትና በማንቀሳቀስ የተጠቀሙና ገንዘብ እንዳሸሹም ተጠቅሷል።

ተከሳሾቹ የጥቁር ገበያን በማስፋፋት፣ የዋጋ ንረት በመጨመር፣ ኢ-ፍታሐዊ የገበያ ውድድር እንዲኖር በማድረግ  በሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብሎ ነው ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ የቀረበባቸው።

ከተከሳሾቹ መካከል 1ኛ ተከሳሽ ብቻ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸውና በንባብ እንዲሰሙ ተደርጓል።

ክሱ በንባብ ከተሰማ በኋላ 1ኛ ተከሳሽ የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅና ላልቀረቡ ተከሾች መጥሪያ እንዲደርስ ለመጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ተቀጥሯል።

 

በታሪክ አዱኛ