አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያውን የሠላም ሥምምነት በመተግበር ረገድ እየወሰደች ያለችውን እርምጃዎች በጄኔቭ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ ልዩ መልዕክተኞች አደነቁ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የደረሱበትን ሥምምነት ለማክበር ያላቸውን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል፡፡
ሥምምነቱን ተከትሎ ግጭት ተከስቶ በነበረባቸው አካባቢዎች መሠረታዊ አቅርቦቶች ሳይደናቀፉ እንዲቀርቡ ከሁለቱም ወገኖች አወንታዊ ምላሾች መታየታቸውም ተመላክቷል፡፡
ኅብረቱ ኢትዮጵያ ሀገራዊ የሽግግር ፍትኅ ሥርዓት ለመተግበር ያሳየችውን ቁርጠኝነትን ያደነቀ ሲሆን ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ አስተማማኝ የሽግግር ፍትኅ እና ተጠያቂነት ወሳኝ ሂደቶች ናቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሽግግር ፍትኅ ሥርዓቱ አተገባበር ላይ ከአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ የሚሻ ከሆነም ኅብረቱ ተሞክሮውን ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሚሼል ቴይለር በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት በተመድ ለተቀመጡት ዓለምአቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች መከበር እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነትን አድንቀዋል፡፡