አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የዓሳ ኃብት በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በቅንጅት መሠራት እንዳለበት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) ገለጸ።
የምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም የሕንድ ውቅያኖስ ክልል የዓሣ ኃብትን የማልማት አቅምን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የኢጋድ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ በምስራቅ አፍሪካ የዓሳ ኃብትን በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተገልጿል።
በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም የሕንድ ውቅያኖስ ክልል በዓሣ ኃብት ልማት የሚሰራው “ኢኮ ፊሽ” ቴክኒካል አስተባባሪ የሆኑት ሱኔል ስዌኒሪ በቀጠናው 50 ቢሊየን ዩሮ የሚተመን የዓሳ ኃብት መኖሩን አመላክተዋል።
ኃብቱን በቴክኖሎጂ አስደግፎ በማልማት ለሀገር ውስጥ ጥቅም እንዲውል እንዲሁም ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ግኝት በማምጣት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በኢጋድ የብሉ ኢኮኖሚና ዓሳ ኃብት ከፍተኛ ባለሙያ ዋሴ ÷ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የዓሳ ኃብት በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል ተጨማሪ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ መንገድ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ግርማ ሙሉጌታ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በዓሳ ዘርፍ ያላትን ኃብት በማልማት ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ኃብት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በዓሳ ኃብት ልማት ተጠቃሚ ለመሆን የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎችን ከሌላ አካባቢዎች ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።